ፍኖተ ሰላም ከተማና ዞናዊ ጉዞዋ

ቅድመ ታሪክ

በቀደመው የመንግስት መዋቅር የጎጃም ክፍለ ሀገር ሰባት አውራጃዎች ነበሩት ፡፡ ከሳበቱ አንዱ የሆነው ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ ዋና ከተማ በመሆን አገለግላለች ፡፡ ዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት “ወጀት” የሚለው ስማዊ ቃል መጠሪያዋ ነበር ፤ የአሁኗ ፍኖተ ሰላም ከተማ ፡፡
ሀገር በአርበኞች እና በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ የዲፕሎማሲ ብቃት ከጣሊያን ወራሪ ነጻ ሲወጣ ፣ ንጉሱ በሲዳን ኦሜድላ በኩል ወደ አዲስ አበባ ገቡ ፡፡ ንጉሱ ካረፉባቸው የጎጃም ቅድመ ግዛቶች መካከል ኦሜድላ ፣ ቻኒ ፣ ወይም ቀሃስ በር እና ፍኖተ ሰላም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ፡፡የዛሬ የጥኩረት መልህቃችንን ፍኖተ ሰላም ላይ አሳርፈናል ፡፡ መንገዱንም የሰላም ያድርገው ፡፡ ”ጎጃም እና አካባቢው ብሎም መላው ኢትዮጵያ ሰላም ነው ፡፡” በማለት ቀዳሚ ኃይለሥላሴ ወጀትን ፍኖተ ሰላም ብለው ሰየሟት ፡፡ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮም ፍኖተ ሰላም የሚለው ስሟ ይፋዊ መጠሪያዋ ሆነ ፡፡

የጃቢ ጠህናን ዋና ከተማ እንዲሁም በራሷ የከተማ አስተዳደር ሆና እስከ 2004 ዓ.ም የዘለቀችው ፍኖተ ሰላም ከ2004 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ለምዕራብ ጎጃም ዞን በዋና ከተማነት ተመርጣለች ፡፡

ፍኖተ ሠላም እና የዞን ከተማነት

ባህር ዳር በራሷ የዞንነት የመዋቅር ደረጃ የተሰጣት በመሆኑና፣ የዞንም ፣ የክልልም ከተማነቷን አጠራቅማ ከምትይዝ ተብሎ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማነቷን ለፍኖተ ሰላም አስረክባለች ፡፡
ፍኖተ ሰላም ከባህር ዳር የተረከበችውን የዋና ከተማት ሚና ከያዘች ሰባት ያህል አመታትን አሳልፋለች ፡፡ ፍኖተ ሰላም ዋና ከተማ ስትሆን ከተማዋ የመልማት እድሏን እንደሚያሰፋላት ተጠብቆ ነበር ፡፡ የተጠበቀው ተስፋ ግን ያን ያህል በውጤት የታጀበ አይደለም የሚል ቅሬታ ከነዋሪዎቿ ይነሳል ፡፡
በንግድ ስራ የሚተዳደረው አቶ አማሳሉ ሺበሺ በሰባት ዓመታት ውስጥ የዞን ተቋማት ተገንብተው ፍኖተ ሰላም በአጭር ጊዜ ውስጥ የዞን አገልግሎት መስጠት መቻሏን ያደንቃሉ ፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ አምሳሉ በመሰረተ ልማት ግንባታና በመብራት አገልግሎት ዘርፍ ከተማዋ ዝቅተኛ እንደሆነች መስክረዋል ፡፡ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ባለሃቶችን ለመሳብ የሚደረገው ቢሮክራሲያዊ አሰራር ዝንፈት እንዳለበትም ገልጸዋል ፡፡
ሌላዋ የከተማዋ ኗሪ ወ/ሮ ትርንጎ እንቢያለ “ፍኖተ ሰላምን የሚመራት አመራር የነዋሪውን ፍላጎት በመሰረተ ልማት ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በስራ ቅጥር ሁኔታ ማሳካት አልተቻለም” ብለዋል ፡፡
አስተዳደሩ ስለ ከተማዋ
የፍኖተ ሰላም ከተማ ምክትል ከንቲባና የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ካሳሁን ነዋሪዎቿ ያነሱትን ቅሬታ ይጋራሉ ፡፡ መብራት የከተማዋ ማነቆ እንደሆነ እና ምላሽ እንደታጣለት የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው ፈጣን እና ዘላቂ ምላሽ በሌሎች የግልጋሎት ለመስጠት ግን አሰራር እየዘረጉ እንደሆነ ተናረዋል ፡፡ ማህረሰብ ተኮር አመራርነትን በመዘርጋት በከተማዋ ልማት ህዝቡ መሪ እንዲሆን እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡ ህዝቡ ለከተማዋ በእኔ ባይነት እንዲሳተፍ የሚገነቡ መንገዶችን እና ሌሎች ስራዎችን ጥራት በተመለከተ ከህዝቡ በተመራ ኮሚቴ ይመራል ፡፡

ከተማዋ የዓለም ባንክ የልማ ፕሮጀክት ተጠቃሚ በመሆኗ በባለፈው 2010 ዓ.ም 59 ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ከዓለም ባንክ በተገኘ ገንዘብ ተሰርተዋል ፡፡በነዚህ ፕሮጀክቶች ይጥራት ችግር በመነሳቱ ጥራቱን ለማስጠበቅ ማህበረሰቡን ያሳተፈ አሰራር በመዘርጋት እየገመገሙ እንደሆነም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል ፡፡ በፕሮጀክቶቹ የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበታልም ይላሉ ፡፡ በ2011 ዓ.ም ወደ 64 ፕሮጀክቶች ገቢራዊ እንደተደረጉም አሳውቀዋል ፡፡ የዓለም ባንክን የፕሮጀክት ገንዘብ በትክክል በመጠቀም ውጤታማዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል ፡፡
በክልሉ ከዓለም ባንክ የሚሰጣቸውን ገንዘብ በትክክል የሚጠቀሙት ውስን ከተሞች ብቻ እንደሆኑ ባለፈው ዓመት ልማት ገልጾ ነበር ፡፡ በ9 ወር ውስጥ ባህርዳር እና ጎንደርን የመሳሰሉት ከተሞች ከተበጀተላቸው ገንዘብ 50 ከመቶውን እንኳን መጠቀም እንዳልቻሉ አመራ ቴሌቪዥን መዘገቡ ይታወሳል ፡፡

ፍኖተ ሰላም እና የባላሃብት ስበት

ከከንቲባው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም 35 የሚሆኑ ባላሃብቶች ለልማት ገብተዋል ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ ሙሉ በሙሉ ግንባታቸውን ቢጨርሱም በመብራት እጥርት ምክንያት ወደ ተግባር አልገቡም ፡፡ 23 ኢንቨስትምንቶች ደግሞ በግንባታ ላይ ሲሆኑ ፤ ሁሉቱ ምንም ያልጀመሩ ናቸው ፡፡ ከሁለቱ አንዱ ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ ተነጥቆበታል ፡፡ በፍኖተ ሰላም ለሚደረገው ኢንቨስትምንት መብራት ችግር በትልቅ ፈተናነት ይቀመጣል ፡፡

መብራት እና የዞኑ ፈተና

በምዕራብ ጎጃም ከባህር ዳር እሰከ ደንበጫ ባሉ ወረዳዎች የተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው ፡፡ በተለይም የቡሬው አግሮ ኢንዱስትሪ በግዝፈቱ በአብነት ይነሳል ፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ስሜነህ አያሌው ለቡሬው ግብርና ተኮር ኢንዱስትሪ በኩታ-ገጠም በየዓመቱ ወደ 9 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ ለኢንዱስትሪው ማምረት መጀመሩን ጠቁመዋል ፡፡
ስንዴንም በኩታ-ገጠም በማምረት ለግብዓትነት እየተዘጋጀ እንደሆነ ዋና አስተዳደሪው ገልጸዋል ፡፡ አቶ ስሜነህ እንደሚሉት ”ፍኖተ ሰላም ከተማን ጨምሮ የምዕራብ ጎጃም የአድገት ማነቆ የሆነው መብራት ነው” ፡፡ ፍኖተ ሰላም የሚገኘው ማከፋፈያ አቅሙ የተዳከመ እና ያረጀ ነው ፡፡ ይህ አሁን ለሚፈጠሩት ኢንቨስትመንቶች ፈተና ሁኗል ፡፡ በቡሬም በተመሳሳይ የማከፋፈያ ችግር አለ ፡፡
በፍኖተ ሰላሙ እና በቡሬው ማከፋፈያ አቅም ከመጨመር/ሰብስቴሽን/ ባለፈ ተጨማሪ ለመገንባት ከመብራት ሃይል ጋር ስምምነት ደርሰናል ያሉት አቶ ስሜነህ በተግባር ደረጃ ግን የተሰራ ስራ እንደሌለ ተናግረዋል ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥያቄያቸውን አጠናክረው በመቀጠል የዞኑን ህዝብ ጥያቄ ለማስመለስ እንደሚተጉ ገልጸዋል ፡፡

በ2009 ዓ.ም መጨረሻ በወጣ ሪፖርት የአማራ ክልል በመብራት ስርጭት ከሀገሪቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚ አይደለም ፡፡ ከ1983 ወዲህ በክልሉ ብዙ የመብራት ማከፋፈያዎች እንዳልተገነቡ የወቅቱ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ለፌደራል መንግስት አሳውቀዋል ፡፡ የመብራት ችግር ዛሬም ለክልሉ በችግርነት ቀጥሏል ፡፡

የግሌ አስተያየት

  • ፍኖተ ሰላምና አካባቢዋ ከፍተኛ የመልማት አቅም አላቸው ለምሳሌ በከፍተኛ ሁኔታ የሰብል ምርት ይመረታል ያውም ስለሌሎች አካባቢዎችም የሚተረፍ። ግን እስካሁን የሰብል ማቀነባበሪያ ፋብሪዎች የሉም (ከቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ በስተቀር)።
  • በመሰረ ልማት ግንባታ በኩል ምንም በበቂ ሁኔታ የለም በሁሉም ዘርፍ። መብራት ደግሞ ትልቁ ህዝቡንና አካባቢን እንዳይንቀሳቀስ ጠርንፎ የያዘ ነዉ ። ምንም መስራት አይቻልም እንኳን ፋብሪዎችን። ስለዚህ ማስፋፊያ ሊሰራ ይገባል እንዴት 30 አመት ካለምንም ማስፋፊያ እንዲቀመጥ ይደረጋል?
  • ሌላው ዋናው ችግር ሙስናና ሌብነት ነው። ፍ/ሰላም ላይ የሚመደቡ የአመራር አካላት በሙሰኝነት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ናቸው። መታወቂያ ሳይቀር የሚሸጡ ናቸው። (በአብርሃም ደምሰው)

ምንጭ፡- በኩር ጋዜጣ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s