ለአማራው ምን ታስቧል?

ሰኔ 15 አማራውን ለማጥቃት ሰበብ ሆኗል። በእርግጥ ሰበብ የሆነው ለብዙዎች እንጅ በክስተቱ ሊጠየቁ የሚገባቸው የፀጥታም ሆነ የፖለቲካ ኃላፊዎች የሉም ማለት አይቻልም። እስሩ ግን በአብዛኛው ያተኮረው ለአማራው ጠቃሚ፣ በክስተቱ ያልነበሩ ሰዎች ላይ ነው።
ሰኔ 15 አጋጣሚ ሆነላቸው እንጅ ገዥዎቹ አማራውን ለማዳከም ሲያቅዱ ቆይተዋል። ሰኔ 15 የተፈጠረውን ለሁለት አጋጣሚ ተጠቅመውበታል።

  • አማራው ክስተቱን ተጠራጥሮ “ገደለ፣ አልገደለም” የሚል ንትርክ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል።
  • በዋነኝነት ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ይቆማሉ ያሏቸውን ለማሳደድ እድል አግኝተዋል። ይህ አጋጣሚ ሲፈለግለት የነበር ጉዳይ ነው። በዋነኛነት:_
  1. የ2011 ዓም ምርጫ ሊደረግም ላይደረግም ይችላል። ሆኖም ኢህአዴግ ውስጥ ምርጫው ካልተደረገ ይለይልናል የሚል ኃይል ተፈጥሯል። ምርጫው ባይካሄድ እንኳ ፖለቲካው ለኢህአዴግ አስጊ ሆኗል። ኢህአዴግ የድሮ ጭምብሉ እየተገለጠ ነው። ይህን የሚያጋልጠው ደግሞ አማራውና ለአዲስ አበባ የቆመ ኃይል (በዋነኝነት ባለ አደራ) ነው። በአዲስ አበባ ጉዳይም የአማራው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ለውጥ ከተባለም በኋላ ገዥዎቹ የሚሰሩትን ደባ በማጋለጥ የአማራውን ያህል ሚና የያዘ የለም። ስለሆነም ምርጫ ተካሄደም አልተካሄደም የአማራው እንቅስቃሴ መቆም አለበት ተብሎ ተወስኗል። ለዛም ነው ስንት ፅንፈኛ እያለ የአማራው እንቅስቃሴ ላይ ወከባና እስር የበዛው።
  2. ምርጫው ከተካሄደ በሚል ለአማራው ሶስት አማራጭ ታስቦለታል። አንደኛውና ዋነኛው የአማራውን ተቋማት ጠፍንጎ ለአዴፓ “ውለታ ውዬልሃለሁ” ማለት ነው። አብን፣ የአማራ ወጣቶች ማሕበርና ሌሎችም እንዲደፈቁና ሌሎች ታዘዥ አደረጃጀቶች እንዲኖሩ ይደረጋል። በአማራው ዘንድ የተጠላው የ”አንድነት ኃይል” አጃቢ ተቃዋሚ እንዲሆን ይታገዛል።
  3. አብን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳ አባላትና አመራሮችን አስሮ አሉባልታዎች እንዲወሩ፣ በአመራሩና በአባላት መካከል መጠራጠር እንዲኖር፣ በዚህ ክፍተት ሌሎች እንዲገቡና ፓርቲውን እንዲያዳክሙ ይፈለጋል።
  4. የታሰሩትን የአማራ ልጆች እንቅስቃሴው ከተዳከመ፣ ወጥተው ተፅዕኖ መፍጠር አይችሉም ብለው ካሰቡ ድርጅቶችንና እንቅስቃሴውን ካዳከሙ በኋላ ቢለቋቸው ምንም አያመጡም ብለው ያስባሉ። አብን ከተዳከመ፣ የሚዲያ ተቋማቱ ከተዘጉ፣ የወጣቶችና ሌሎች አደረጃጀቶች ከተዳከሙ አማራውን አደራጅቶ ውድድር ውስጥ ከማስገባት ተስፋ መቁረጥ ይሆናል እጣው ብለው አስበዋል።
  5. አማራው ተቋማቱ ቢዳከሙም ከእስር የሚፈቱት፣ የሚዋከቡት እድል ካገኙ ሕዝብን መያዝ ይችላሉ ብለው ካሰቡ ምርጫው ሲቃረብ፣ ምንም ለማድረግ ጊዜ አይኖራቸውም ብለው ባሰቡበት ጊዜ ከእስር እንዲፈቱ ያደርጉና አጀንዳ ያደርጉታል። “ፈታንላችሁ” ብለው ሕዝብን “እልል” ለማሰኘት ይጥራሉ። ሕዝብ ተቀይሞ ቢሆን እንኳ ምርጫው ሲደርስ ቢፈቱም ሕዝብ እንደውለታ የሚቆጥርላቸው ይመስላዋል።
  6. “የፈለገ ይሁን” ብለው ካሰቡ፣ የአማራ ትግል ላይ ያላቸው ጥላቻ በወቅታዊ ጉዳይ ተጠቅመን የምንተወው አይደለም ካሉ ደግሞ ከምርጫው በኋላም ቢሆን እያየን እንፈታለን ብለው ያስባሉ። ካልሆነ እስከወዲያኛውም ማፈን እንችላለን የሚል ስሌት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።

በዚህ ሁሉ የገዥዎች ስሌት ግን አዴፓ የከፋ መጠላት ውስጥ እንደሚገባ መገመት አያዳግትም። በዚህ ሁሉ ሴራና ፀረ አማራ እቅድ ውስጥ ግን አማራው የባሰ በገዥዎቹ ላይ ቂም ይይዝ እንደሆነ እንጅ ጣል እርግፍ አድርጎ የሚጥለው አጀንዳ እንደሌለ መገመት አይከብድም። በዚህ ሁሉ ሴራ ውስጥ፣ በዚህ ሁሉ የገዥዎች አማራው ላይ መልፋት መሃል ኢትዮጵያ ትጎዳ ካልሆነ በስተቀር የአማራው ትግል ከምንም አይነት አፈና፣ ከየትኛውም የገዥዎች እቅድ፣ ከየትኛውም የውስጥ ድክመት፣ ከመደፈቅና ከመታፈን በኋላ አፈር ልሶም ቢሆን እንደሚነሳ መጠራጠር አይቻልም! ያኔ የአማራው ትግል ተመልሶ ሲነግስ ግን እንደ ባለፈው ለገዥዎች የድጋፍ ሰልፍ የሚያደርግ፣ የራሱን አስገዥዎች የሚምር አይመስለኝም!

በጌታቸው ሽፈራው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s