ፍኖተ ሠላም ከተማ የሚገኘው የላህ ወንዝ ተለዋጭ ድልድይ ጥራት ችግር ጉዳይ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ግን ድልድዩ አሳሳቢ አለመሆኑን በመግለጽ የአጠቃላይ መንገዱ ማሻሻያ ዲዛይን እየተሠራ መሆኑን አስውቋል፡፡

የምዕራብ ጎጃም ዞን ርዕሰ ከተማ ፍኖተ ሠላም በተነሳች ቁጥር በነጭ እና ጥቁር ቀለማት አሸብርቆ የሚታየው የግማሽ ክብ ቅርጽ የ80 ዓመቱ የላህ ወንዝ ድልድይ ይወሳል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከቅርጹ በመነሳት ‹‹ቀስተ ደመና›› የሚል ስያሜ ተሰጥተውታል፤ ለድልድዩ። ድልድዩ የተሠራው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣችበት ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት ነው።
በቅርቡ የዚህን ነባር ድልድይ ጫና ለመቀነስ ተለዋጭ ድልድይ ተገንብቶ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች አዲሱ ድልድይ ጥራት ላይ ቅሬታ እያነሱ ነው። አቶ ተፈራ ዋሴ ይባላሉ። የ83 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው። “ድልድዩ ሲሰራ በዓይኔ አላየሁትም። ነብስ ካወኩ ጀምሮ ግን አውቀዋለሁ። ከልጅነት እስከ ሽምግልና ዘመኔ እያየሁት ነው። አሠራሩ ጥንቃቄ የተሞላበት ስለሆነ ለዚህ ዘመን በቅቷል” ብለውናል ስለ ነባሩ ድልድይ።
በቅርብ ጊዜ የተሠራዉ ተለዋጭ ድልድይ መፈረካከስ መጀመሩን እንደ መነሻ በማድረግ እንደ ነባሩ ጥንካሬ የሌለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የድልድዩ አሠራር የጥራት ችግር ስላለበት ክረምት ውኃ ማቆሩን እና መሰነጣጠቅ መጀመሩን በማንሳት የአቶ ተፈራ ዋሴን ስጋት ይጋራሉ፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደብረ ማርቆስ መንገድ ‹ኔትወርክ እና ሴፊቲ ማኔጅመንት› (ትስስርና ደኅንነት አስተዳደር) ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥሩነህ አዱኛ ድልድዩ የውኃ ማፋሰሻዎች ቢያንሱትም ስጋት ላይ የሚጥል ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል። ድልድዩ ነባሩን ድልድይ በአዲስ መልክ ለመገንባት ታቅዶ በነበረበት ወቅት እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ በጊዜያዊነት የተሠራ መሆኑን ኢንጂነር ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡ በጊዜያዊነት የተገነባው ድልድይ ቋሚ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸው ለአደጋ የሚያጋልጥ ችግር እንደሌለበትም አመልክተዋል፡፡
ከደብረ ማርቆስ እስከ ባሕር ዳር ያለውን መንገድ ስፋት ለማሻሻል የዲዛይን ሥራ እየተሠራ እንደሆነ እና ዲዛይኑም ወደ መጨረሻው እንደደረሰም አስታውቀዋል። ድልድዩ የሚያሰጋ ችግር ባይኖርበትም የበለጠ ለማረጋገጥም በአዲሱ ዲዛይን ሊታይ እንደሚችል አስታውቀዋል።

አብመድ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s