የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ የብድር ዕዳ 1.5 ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተገለፀ – ሪፖርተር

  • እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም. ድረስ ያለው የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭና የአገር ውስጥ ብድሮች ዕዳ 1.5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ብድር ዕዳ 111.9 ቢሊዮን ብር ነው
  • የሌሎቹ የልማት ድርጅቶች የውጭና የአገር ውስጥ አጠቃላይ የብድር ዕዳ 594 ቢሊዮን ብር ደርሷል
  • ማዕከላዊ መንግሥትና የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልመለሱት ዕዳ 412.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል
  • መንግሥት ከንግድ ባንክ የወሰደውን ብድር መመለስ ባለመቻሉ በየዓመቱ እስከ 25 ቢሊዮን ብር ወለድ እየከፈለ ነው

የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮችን የዕዳ መጠን የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ፡፡

ሪፖርተር ከሚኒስቴሩ ያገኘው ዝርዝር የዕዳ መግለጫ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ አገሪቱ እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያለባት ያልተከፈለ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ 1.5 ትሪሊን ብር ወይም 52.57 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡
ከተጠቀሰው አጠቃላይ የአገሪቱ ዕዳ ውስጥ 26.93 ቢሊዮን ዶላር ወይም 769.08 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ የውጭ አበዳሪዎች ተገኝቶ ያልተከፈለ ዕዳ ሲሆን፣ የተቀረው 730.5 ቢሊዮን ብር ወይም 25.6 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ከአገር ውስጥ የመንግሥት ባንኮች ማለትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፣ እንዲሁም ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና (ጡረታ) ፈንዶች ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡

አገሪቱ ካለባት የውጭ ዕዳ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥት (Centeral Government) ዕዳ 449.7 ቢሊዮን ብር (15.73 ቢሊዮን ዶላር) ሲሆን፣ ቀሪው 319.3 ቢሊዮን ብር (11.17 ቢሊዮን ዶላር) ደግሞ የተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መንግሥት በገባላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ (Loan Guarantee)፣ ሌሎች ሁለት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ፣ በራሳቸው ከውጭ አበዳሪዎች በቀጥታ ተበድረው ያልከፈሉት ዕዳ ነው፡፡

ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ ከውጭ የተበደሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም መሆናቸውን ያመላከተው መረጃው፣ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ከውጭ አበዳሪዎቻቸው ያለ መንግሥት ዋስትና በቀጥታ ተበድረው እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያልከፈሉት ዕዳ 3.9 ቢሊዮን ዶላር ወይም 111.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሎሎቹ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገቡላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ በመጠቀም ከወሰዱት የውጭ ብድር ውስጥ እስከ ማርች 2019 ድረስ ያልከፈሉት የዕዳ መጠን 207.38 ቢሊዮን ብር (7.27 ቢሊዮን ዶላር) መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ ከላይ የተገለጸው እስከ ማርች 2019 ድረስ አገሪቱ ያለባትን አጠቃላይ የውጭ ብድር ዕዳ የሚያመለክት ሲሆን፣ እስከተገለጸው እ.ኤ.አ. ተመሳሳይ ወቅት ድረስ የተመዘገበው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ዕዳ ደግሞ 730.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃው ያመለክታል፡፡

ሪፖርተር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s