የኦሮሞ ህዝብ፣ ODPና ፣ የዶ/ር አብይ መንግስት የማይፈልጉት፣ እነሱን የማይጠቅም፣ ይልቁንም ልክ እንደ ህወሀት፣ እነሱን የሚያስጠላ ድርጊት፣ በአንዳንድ መርማሪ ፖሊሶች እየተከወነ ነው። (በቹቹ አለባቸው)

“የኦሮሞ ህዝብ፣ ODPና ፣ የዶ/ር አብይ መንግስት የማይፈልጉት፣ እነሱን የማይጠቅም፣ ይልቁንም ልክ እንደ ህወሀት፣ እነሱን የሚያስጠላ ድርጊት፣ በአንዳንድ መርማሪ ፖሊሶች እየተከወነ ነው።”
(በቹቹ አለባቸው)

ህወሀትን የበለጠ ያስጠሉት እነማን ናቸዉ?
ህዉሀት በተፈጥሮዉ፣ በጥላቻ ላይ በተለይም በአማራ ጥላቻ ላይ ተመሰርቶ የተፈጠረ ድርጅትና በርካታ ስህተቶችን የፈፀመና ያስፈጸመ ድርጅት ቢሆንም፣ ባለፉት 27 አመታት የተፈጸሙትን ሁሉንም ስህተቶችና ወንጀሎች፣ ህወሀት እንደ ድርጅት እያወቀና ቀጥተኛ ትዕዛዝ እየሰጠባቸዉ የተፈጸሙ ነበሩ ብየ አላምንም። ምክንያቱም፣ በህወሀት ስም ሲፈፀሙ ከከረሙት ከአንዳንዶቹ ጭካኔ የተሞላባቸዉ ወንጀሎች፣ አይደለም የትግራይ ህዝብ ህወሀትንም የሚጠቅሙ አልነበሩም/አልጠቀሙምና።
በእኔ እምነት፣ ህወሀት በራሱ ፍቃድና ሙሉ እዉቅና ለፈጸማቸዉ ሰህተቶች ዛሬም ባይሆን ነገ መጠየቁ አይቀርም። ነገር ግን አንድ ልብ መባል ያለበት ነገር አለ። ህወሀትን እንዲህ በፍጥነት ከመድረክ እንዲገፋ ያደረጉት፣ የራሱ ቀጥተኛ ስህተቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በየመንግስት መስሪያ ቤቱ ተሰግስገዉ፣በህወሀትና ትግራይ ህዝብ ስም ሲነግዱ የከረሙና የራሳቸዉን ጥቅም ሲያሳዱ የከረሙ አንዳንድ አባሎቹ ስህተት ጭምር ነዉ ። በተለይም በደህንነት፣ በፖሊስ፣ በመከላከያ መዋቅር የከረሙ አንዳንድ ስግብግብና ፣ ዘላለማዊ ነን ብለዉ ያስቡ የነበሩ ወገኖች ዋነኞቹ ችግር ፈጣሪ ነበሩ። በነዚህ ወገኖች መጥፎ ስራ የተነሳ፣ የትግራይን ህዝብ ለጥርጣሬ፣ ህወሀትን ደግሞ ከድሮዉ በበለጠ እምነት የማይጣልበትና በሌሎች ዘንድ የተጠላ ድርጅት ሆኖ እንዲታይ አደረጉት።

የዶ/ር አብይና ODP ነገርስ?

ዛሬ ይሄን ጉዳይ ለመጻፍ የተገደድኩት፣ ነገሮች እየተደጋገሙ ስለሆነና፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከመለጠፍ ይልቅ፣ ጉዳዩን ለአዴፓ አመራር በአካል ለማስረዳት ፍላጎቱ ስለነበረኝ ነዉ(ሞክሪያለሁ)። ሆኖም ባሰብኩት ልክ አልተሳካልኝም፣ ሰሚ ካገኘሁና የአዴፓ አመራር ለመስማት ጊዜ ካላቸዉ፣ ስለተገነዘብኩት ጉዳይ በዝርዝር እነግራቸዋለሁ።
ነገሩ እንዲህ ነዉ። የሰኔ 15ቱን ክስተት ተከትሎ፣ በርካታ አማራወች ፣ በተለይም በባ/ዳር፣ በአዲስ አበባና በኦሮምያ ክልል አንዳንድ አካባቢወች ፣ ከድርጊቱ ጋር ተጠርጥራችሁዋል ተብለዉ በጀምላ መታሰራቸዉን እናዉቃለን። የተፈቱ ቢኖሩም ዛሬሞ በርካቶች እስር ላይ ናቸዉ።
በአንድ ነገር እንግባባ። ማንኛዉም አማራ ህግ ማክበር አለበት፣ህግን በመተላለፉ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ቢወስድበት፣ አማራነትን ምሽግ ማድረግ አይችልም። አማራነት ምሽግ የሚሆነዉ ለህጋዊያን ብቻ ነዉ። ምን ለማለት ፈልጌ ነዉ፣ በእዉነት ህግን የተላለፈ ካለ ጠበቃ አንቆምም ለማለት ነዉ። በአንጻሩ ደግሞ ፣ ህግን ሰበብ አድርጎ ፣ ማንነትን ወይም ፖለቲካዊ አመለካከትን መሰረት አድርጎ የሚደርሰን ጥቃት እናወግዛለን ለማለት ነወ።
ነገሩን ግልጽ ላድርገዉ። በአሁኑ ወቅት በተለይም በአዲስ በርካታ አማራወች በእስር ላይ ናቸዉ። የእስራቸዉ ምክንያትም ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር የተያያዘ ነዉ የሚል ነበር። በወቅቱ ምንም እንኳን ቢያንስ በቅርብ ከማዉቃቸዉ መካከል እንደነ በለጠ ካሳ በዚህ መጠርጠራቸዉ፣ ስለተከሰሱበተ ነገር ጥርጣሬ ጭሮብኝ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ጉዳዩ ከባድ ስለነበር፣ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ መቆየቱን መርጨ ነበር። ልጆቹ ለጊዜዉ ቢታሰሩም፣ በሂደት እዉነቱ እንደሚወጣም ስለማምን።
ይሄ ሁኔታ በዚህ እንዳለ፣ ልጆቹ እስር ቤት እያሉ የሚወጡ መረጃወች የሚረብሹ እየሆኑ መጡ ። በተለይም የተቀላጠፈ ፍትህ አለማግኘት፣ ተጠርጥረዉ የታሰሩበት ወንጀልና ፣ መርማሪ ፖሊስ ጠየቃቸዉ የሚባሉትን ነገሮች ስንሰማ፣ ዉጭ ያለነዉ ወንድም/እህቶቻቸዉ፣ ስለጉዳዩ ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን።
እስረኞቹ መርማሪ ፖሊሰስ፣ ከተጠረጠርንበት ወንጀል ባፈነገጠ መልኩ፣ ከነገሩ ጋር የማይገናኝ ጥያቄ እየጠየቀን ነዉ ብለዉ ተናገሩ የሚሉ መረጃወች መዉጣት ከጀመሩ ሰነባበቱ። እኔም መጀመሪያ ላይ ፣ የተለመደዉ የfb ወሬ ይሆናል ብየ መጀመሪያ ላይ ነገሩን ቸላ አልኩት። ነገሩ ግን እየገፋ መጣ። እሄኔ እኔዉ ራሴ በአካል ተገኝቸ ነገሩን ማረጋገጥ እንደሚሻል ስላመንኩ፣ ከወደ5 ቀን በፊት ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣብያ አመራሁ። ለመረጃ የምፈልጋቸዉን ልጆች አገኘሁ። እዉነቱን እንዲነግሩኝ ጠየቅኳቸዉ፣ በሙሉ ልብነት ግጥም አድርገዉ ነገሩኝ። አዘንኩ። የህወሀት ሰወች የሰሩት ስህተት፣ ዛሬም ላይ እየተደገመ መሆኑን ተገነዘብኩ።
የኦሮሞ ህዝብ፣ ODPና ፣ የዶ/ር አብይ መንግስት የማይፈልጉት፣ እነሱን የማይጠቅም፣ ይልቁንም ልክ እንደ ህወሀት፣ እነሱን የሚያስጠላ ድርጊት፣ በአንዳንድ መርማሪ ፖሊሶች እየተከወነ መሆኑ ገባኝ። ሰዉ እንዴት ከህወሀት መጠላትን አይማርም? ይሄ ድርጊትስ ታላቁን የኦሮሞን ህዝብ በማያዉቀዉ ነገር ከማስጠላት፣ የODPን ተቀባይነት የበለጠ ከመሸርሸር፣ በተለይም በዶ/ር አብይንና መንግስታቸዉ ላይ እየተዳከመ የመጣዉን የመታመን ችግር የበለጠ ከማባባስ ዉጭ ምን ጥቅም ይኖረዋል? ስል ራሴን ጠየቅኩ።
ለሁሉም ከጣቢያ እንደወጣሁ፣ ለአንድ የአዴፓ ባለስልጣን ደወልኩ፣ አልተመቸዉም ነበርና ስልክ አላነሳም። እኔም ቢያንስ አዴፓ ጉዳዩን አዉቆ ጉዳዩን እንዲከታተለዉ አጭር መለዕክት ላኩለት። መለሰልኝ፣ መልሶ እንደሚደዉል አሳወቀኝ። አልተመቸዉም መሰለኝ እስካሁን አልደወለም። መደወል ነበረበት፣ ምክንያቱም ጉዳዩ የሚረሳ አልነበረም።

አዴፓ ከወዴት ነህ?

በአንድ ጉዳይ በጽኑ አምናለሁ። አማራ ስለሆነ ብቻ ማንም ወንጀል ለፈጸመ ሁሉ አዴፓ ጣልቃ ይግባ አልልም። እንዴዉም በግንባር ቀደምትነት ህግ እንዲከበር መሰራት አለበት። ነገር ግን ሰበብ ተፈልጎ ሰዉ በአማራነቱና በያዘዉ ፖለቲካዊ አመለካከት የሆነ አማራ ሲጠቃ አዴፓ ዝም ብሎ መመልከት አይገባዉም። አይደለም ማንም ፖለቲካዊ ተሳትፈበ የሌለዉ አማራ፣ በተቃዋሚነት የሚታወቀዉ አብንና አባላቱም ቢሆኑ፣ ማንነታቸዉንና ፖለቲካዊ አመለካከታቸዉን መሰረት ተደርጎ የሚደርስባቸዉን ጫና ፣ አዴፓ መከላከል አለበት ብየ አምናለሁ።
ADP ከ ODP ጋር መልካም ግንኙነቴ እንዳይበላሽ ብሎ፣ መታለፍ የሌለባቸዉን ስህተቶች ማለፍ የለበትም። ወዳጅነት በመከባበር ላይ ሲመሰረት ነዉ የሚያምረዉ። ዛሬ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በአብን አመራሮችና አባላቱ፣ እንዲሁም ፣ በስቪክ መሪወች፣ በአጠቃላይ በማንኛዉም አማራ ላይ፣ ህግን ከለላ በማድረግ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚወሰዱ እርምጃወችን፣ አዴፓ ማስቆም ካልቻለ፣ ነገ ጥቃቱ ወደራሱ የመዞር እድሉ ዝግ እንዳልሆነ አዴፓ ማወቅ አለበት። ምክንያቱም ፣ ልክ እንደሌላዉ አይነት ፍቅር፣ ድርጅታዊ ፍቅርም ያረጃልና። ለዚህ ጥሩ ማሳያዉ የሚሆነዉ ደግሞ፣ እንደ ግለሰብ የሟቹ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ታምራት ላይኔን ነገር ማስታወስ ነዉ። እንደ ድርጅት ደግሞ የህወሀትና የብአዴንን ነገር ማሰብ ነዉ።
በርግጥ ፣ በዚህ በኩል አዴፓ ያደረጋቸዉን ጥረቶች አልክድም። በተለይም በኦሮምያ ክልል ታስረዉ የነበሩ አማራወችን ለማስፈታት፣ የአዴፓ አመራር ያደረገዉን ጥረት ሰለማዉቅ፣ መካድ አልችልም። ነገር ግን በተለይ አዲስ ላይ የአዴፓ በተለይም የአዲስ አዴፓ አመራር ዝምታ ልክ አይደለም። ወንጀል የሰራ አማራ በህግ መጠየቅ እንዳለበት የምናምነዉን ያክል፣ ተገቢ ባልሆነና በማንነት ዙሪያ ላይ ተመስርተዉ የሚስተዋሉ ሰህተቶችን መታገል ደግሞ ከአዴፓ አመራር በተለይም ከአዲስ አዴፓ አመራር ይጠበቃል ባይ ነኝ።

መፍትሄ

  1. የኦሮሞ ህዝብ፣ ODP እና ዶ/ር አብይና መንግስታቸዉ፣ በህወሀት ዘመን የታየ ስህተት ዛሬም እየተደገመ መሆኑን ግንዛቤ ወስደዉ፣ ሰህተት ፈጻሚወቹን፣ ከወዲሁና ነገሩ በጣም ሳይበለሻሽ፤ በስማችን አትነግዱ ሊሏቸዉ ይገባል።
  2. አዴፓ- ነገር እየተበላሸ መሆኑን አዉቆ ከODP ጋር በመምከር ፈጥኖ ማስተካከል ቢችል ጥሩ ነዉ። ያለበለዝያ ነገሩ ለራሱ ለአዴፓ ጥሩ አይሆንም። ከዚህ ጋር አያይዞ አዴፓ አንድ መሰረታዊ ጥያቄን ቢያጠናዉ ጥሩ ነዉ። ይሄዉም አማራ በህወሀት ዘመን በማንነቴ የተነሳ ስጠቃ ነበር ብሎ በማመኑ፣ ታግሎ ነገሩን የቀየረ መስሎት ነበር። ነገር ግን ዛሬም ይህ ጉዳይ እንደገና እያገረሸ ነዉ። አዴፓ ምክንያቱ ምንድን ነዉ ብሎ ያምናል? ህወሀትስ አዴፓን ሰለሚንቅ፣ ያን አደረገ እንበል። ይህ ነገር እየተደገመ ያለዉ፣ ዛሬም ቢሆን ODP አዴፓን አያከብርም/አይፈራም ማለት ይቻል ይሆን? ይሄ ከሆነ ችግር ነዉ።
  3. አብን:- በተለይም በዚህ ወቅት አዴፓ ጋር ያለዉን ግንኙነተ ሊያሻክሩ ከሚችሉ፣ መግለጫወችና ንግግሮች ቢቆጠብ ስል እመክራለሁ። ለምሳሌ አብን፣ አዴፓን የአማራ ህዝብ “ጀኒዉን ወኪል ነዉ ብሎ አያምንም” የሚል አባባል የሚጠቅም አይመስለኝም።አባባሉ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን ያጠናክራል። አዴፓም በዚህ አባባል እልህ ዉስጥ ሳይገባ፣ ነገሮችን በሆደ ሰፊነት በመመልከት፣ ከአብን ጋር የጀመረዉን አብሮነት መቀጠል ቢችል የተሻለ ነዉ እላለሁ።
  4. ”የአማራ አክቲቪስቶች” እስኪ ልብ ግዙ!

መልካም ሰንበት!!!!!!!

Leave a comment