አማራ ነኝ

‹‹ አማራ ነኝ ››
—›
አማራ ነኝ…
እንደ ቴዲ – ብርቱ ጉልበቴ፤
እንደ ገብርዬ – ኮስታራ አሞቴ፤
እንደ በላይ – ማይስት ጥይቴ፤
እንደ እምዬ – ሩህሩህ ልቤ፤
እንደ ፋሲል – ጠንካራ ግንቤ…!
~
አቋቋሜ – ደጀን ተራራ፤
አተያዬ – ንሥር አሞራ፤
በበላይ ወኔ – ጓንዴ ታጥቄ፤
በገብርዬ ክንድ – ጦሬን ሰብቄ፤
ሀገር ምጠብቅ – ጠላት ምመታ፤
የሕዝብ ትምክህት – ያገር አለኝታ…!
~
አማራ ነኝ…
እንደ አምደ-ጽዮን – ርስቴ ሰፊ፤
እንደ ተዋነይ – ቅኔ ዘራፊ፤
እንደ ተክሌ – ዜማ ቀማሚ፤
እንደ አካለ ወልድ – መጽሐፍ ተርጓሚ፤
እንደ ሼህ ሁሴን – ትንቢት ነጋሪ፤
እንደ ደሼት – ኮከብ ቆጣሪ…!
~
አማራ ነኝ…
የዓይኔ ብሌን – ኢትዮጵያን ሥሎ፤
የልቤ ከፍታ – ሀገር አክሎ፤
ግራ ቀኝ እጄ – ሰንደቋን ሰቅሎ፤
እንደ ዳሽን – ከፍ ያለ ልቤ፤
እንደ ጣና – ሰፊ ሐሳቤ፤
እንደ ዓባይ – ረዥም መንገዴ፤
እንደ ሰብለ – ጽኑ መውደዴ…!
~
ለወዳጄ – ታማኝ ፍቅረኛ !
ለጠላቴ – ክፉ መጋኛ !
ለጠቢባን – የቅኔ መምህር !
ለእኩያን – የቅጣት በትር !
~
አኗኗሬ – ድንበር ማያጥረኝ፤
ጎጃም ብወለድ – የትም የምገኝ !
ፍልስፍናዬ – ፍቅር እና ሥራ፤
ከመላእክት – እምነት ምጋራ !
~
አማራ ነኝ – እንደ አባቶቼ፤
ጎጆ ቀልሼ – ሀገር ገንብቼ፤
ለዳር ድንበሯ – ደሜን ገብሬ፤
ለኗሪዎቿ – ሰላም ፈጥሬ…!
ለነፃ ምድር – ሌት ቀን ምለፋ፤
ባጭር ቁምጣዬ – ሀገር ምሰፋ።
~
ለሚወደኝ – ፍቅር ለግሼ፤
ለበደልሁት – በሬዬን ክሼ፤
ክብሬን ለሚደፍር – ልኩን ሰጥቼ፤
በብርቱ ክንዴ – ምቆም ጸንቼ…!
~
አማራ ነኝ – የእነ በላይ ዘር፤
ግራ እጄ ሞፈር – ቀኜ ዲሞትፈር፤
ለተራበ – የጤፍ እንጀራ፤
ለጠገበ – ኮሶ መራራ…!
~
ለኢትዮጵያ – ዋልታና ማገር፤
ለሕዝቦቿ – ማሰሪያ ፍቅር፤
ለጠላቷ – ብርቱ ራስ ምታት፤
ለወዳጇ – የሰላም ብርታት…!
~
አማራ ነኝ – የጽንዓት አድባር፤
ያ’ገር አለኝታ – ያብሮነት አውጋር፤
የማልመኝ – ከአንድነት ሌላ፤
ያገር ጠላት – ባይኔ ማይሞላ፤
በጠባቦች – ደሜ ሚፈላ፤
ለተራማጅ – ጥላ ከለላ…!
~
መርዝ ቢዘራ – ጠባብ ጎጠኛ፤
ይቅር ብየው – ሰላም ምተኛ፤
ንቀቴን ፍርሃት – አርጎ ለሚወስድ፤
የምነሳበት – እንደሳት ነደድ…!
~
አማራ ነኝ…
ከእነ አሉላ – ከአብዲሳ አጋ፤
በጋራ ምቆም – ጠላት ልወጋ፤
ጀግናን ለማክበር – ክልል ማላጥር፤
ለሕይወት አጋር – ዘር የማልቆጥር፤
ለአንድነት ምሥጢር – ጥበብ ቀምሬ፤
ለሰንደቅ ክብር – ፍቅር ዘምሬ….
~
አማራ ነኝ…
እንደ ጎጃም…
በቋንቋው ደራሽ – ጀግና አርበኛ፤
እንደ ጎንደር…
ሀገርን ቀያሽ – ብርቱ ጦረኛ፤
እንደ ወሎ…
ኑሮን አካፋይ – ፍቅር ቀማሪ፤
እንደ አገው…
አለትን ፈልፋይ – መቅደስን ሠሪ፤
እንደ ሸዋ…
ሀገር ሠዓሊ – መንግሥት ዘዋሪ…!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s